ማቲዎስ ወንዱ ፋውንዴሽን ለዲ.ኤች.ኤል ኢትዮጵያ ሰራተኞች ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞችን ስለመከላከልና በጊዜ ምርመራ በማድረግ ስለመታከም ትምህርት ሰጥቷል፡፡ በየዓመቱ የጡት ካንሰር ወርን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ ተቋማት የሚደረገው የኝዛቤ ማስጨበጫና የትምህርት መርሐ ግብርተላላፊ ያልሆኑ ህመሞች ላይ በማተኮር ከጥቅምት ወር ባለፈ ቀጥሏል፡፡
ለዲ.ኤች.ኤል ሰራተኞች በተዘጋጀው የግዛቤ ፕሮግራም ላይ ባለቤታቸው ወ/ሮ ገነት ብርሀኑን በጭንቅላት ካንሰር ህመም በሞት ያጡት አቶ አለማየሁ” የኔን ቤት ጭር ያደረገውን ካንሰር ለመበቀል ከማቲዎስ ወንዱ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ማህበረሰቡን ስለቅድመ ምርመራ ለማስተማር ተዘጋጅቻለሁ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የማቲዎስ ወንዱ ፋውንዴሽን ማህበራዊና ስነልቦናዊ ድጋፍ ማዕከል ሐኪም ዶ/ር ቬሮኒካ ዝናቡ ለዲ.ኤች.ኤል ሰራተኞች ተላላፊ ስላልሆኑ ህመሞች፣ አጋላጭ ምክንያቶቻቸው፣ እንዲሁም ቅድመ ምርመራና ህክምና ያላቸውን ጠቀሜታዎች በተመለከተ ሰፋ ያለ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡
ከዘጠኝ ዓመት በፊት ደረጃ ሁለት የጡት ካንሰር ተገኝቶባት ህክምናዋን በአግባቡ በመከታተል መዳኗን ለሰራተኞቹ የገለፀችው ወ/ሮ ትዕግስት በህክምና ሂደቷ የአቶ ወንዱ በቀለ መልካምነትና የፋውንዴሽኑ ዕገዛ እንደረዳት ተናግራለች፡፡ በፋውንዴሽኑ ማህበራዊና ስነልቦናዊ ድጋፍ ለመዳን የበቃን ሰዎችና አሁንም ድጋፍ እየተደረገላቸው ያሉ ህሙማንና ቤተሰቦቻቸው አቶ ወንዱን ሁሌም እናስባቸዋለን ስትል ግልጻለች፡
የዲ.ኤች.ኤል ኢትዮጵያ ሰራተኞች ፋውንዴሽኑ ጤናቸውን እንዲጠብቁ ትምህርት ስለሰጣቸው አመስግነው በቻሉት ሁሉ ለካንሰር ህሙማኑ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
ማቲዎስ ወንዱ ፋውንዴሽን የወ/ሮ ገነት ብርሀኑ ቤተሰቦች የደረሰባቸውን ጥልቅ ሃዘን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ካንሰርና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞችን ለመከላከል ላደረጉት ድጋፍ ላቅ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል።
Recent Comments