የአዲስ አበባ ምግብ መድሃኒት ባለስልጣን አመራርና ሰራተኞች በአቶ ወንዱ በቀለ ቤት በመገኘት ቤተሰብና ወዳጅ ዘመዶቻቸውን በማፅናናት አቶ ወንዱ የጀመሯቸውን ስራዎች ለማስቀጠል ከቤተሰብና ከድርጅታቸው ጎን እንደሚቆሙ ገለፁ፡፡
የአዲስ አበባ ምግብ መድሃኒት ባለስልጣን አመራርና ሰራተኞች በአቶ ወንዱ የቀብር ሥነሰርዓት ላይ የአበባ ጉንጉን ያኖሩ ሲሆን በድጋሚ በአቶ ወንዱ መኖሪያ ቤት በመገኘት ቤተሰቦቻቸውን አፅናንተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ምግብ መድሃኒት ባለስልጣን ዋና ሥራአስኪያጅ ወ/ሮ ትዕግስት በዳዳ በአቶ ወንዱ በሞት መለየት የተሰማቸውን ሀዘን በመግለፅ አቶ ወንዱ ለህዝባቸው ጤና በመቆርቆር ላለፉት 22 ዓመታት ብዙ ውጤታማ ስራዎችን የሰሩ ታላቅ ሰው መሆናቸውን መስክረዋል፡፡ የተጀመሩ ሥራዎች እንዲቀጥሉ የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ ተቋሙም ከድርጅታቸውና ከቤተሰባቸው ጎን እንደሚቆም ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ምግብ መድሃኒት ባለስልጣን አመራርና ሰራተኞችን በመወከል ለቤተሰቡ የማፅናኛ መልዕክት ያስተላለፉት አቶ እንጋ እርቀታ ባለስልጣኑ የቁጥጥር ዘርፍ ም/ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንዱ ከባለስልጣኑ ጋር በጋራ በመሆን በርካታ ውጤታማ ሥራዎችን መስራታቸውን ገልፀው በተቻለ አቅም ሁሉ ከድርጅታቸው ጎን በመቆም የጀመሯቸው ሥራዎች የማህበረሰቡን የህመም ጫና የሚያቃልሉ በመሆናቸው ለማሳካት ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
የማቲዎስ ወንዱ ፋውንዴሽን ጊዜያዊ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዘላለም መንግስቱ የባለስልጣኑን አመራርና ሰራተኞች አመስግነው። ወደፊትም የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በመግለፅ ለሚደረግላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።
የአቶ ወንዱ ባለቤት ወ/ሮ አምሳለ በየነ በአቶ ወንዱ በቀለ ከዚህ ዓለም መለየት ሀዘናቸውን በተለያየ መንገድ እየገለፁ የሚገኙ ተቋማትና ግለሰቦች በርካታ መሆናቸውን በመግለጽ ሁሉንም ያመሰገኑ ሲሆን አቶ ወንዱ ላለፉት 22 ዓመታት የካንሰርና ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞች ላይ ህክምና የሚያደርጉ ህሙማንና ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡ እስከ ህይወታቸው ፍጻሜ ጤናማ አፍሪካ የተሰኘው ፕሮጀክት እውን ሆኖ የማየት ጉጉት ስለነበራቸው ይህንን ለማሳካት ሁሉም ሰው እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበው በመኖሪያ ቤታቸው በመገኘት ያጽናኗቸውን የአዲስ አበባ ምግብ መድሃኒት ባለስልጣን አመራርና ሰራተኞች አመስግነዋል፡፡
Recent Comments