ማቲዎስ ወንዱ ፋውንዴሽን 22ኛ የምስረታ በዓሉን አክብሯል።

በ4 ዓመቱ በደም ካንሰር ምክንያት ከዚህ ዓለም የተለየውን ህፃኑን ማቲዎስ ማዳን ባይቻልም ብዙ ማቲዎሶችን እናድናለን በሚል የተቋቋመው ማቲዎስ ወንዱ ፋውንዴሽን ላለፉት 22 ዓመታት ህሙማንን በመርዳትና ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞችን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ብዙ አስተዋፅኦ ማበርከቱን የማቲዎስ አባትና ከፋውንዴሽኑ መስራቾች አንዱ የሆኑት የማቲዎስ ወንዱ ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወንዱ በቀለ ተናግረዋል።

አቶ ወንዱ የካንሰር ህመም ታማሚ መሆናቸው ከተለየ በኋላ ከአንድ ዓመት በላይ በውጭና በሀገር ውስጥ ህክምናቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ሲሆን የፋውንዴሽኑ 22ኛ ዓመት ሲከበር በአሁኑ ሰዓትም ህክምናቸውን በአግባቡ እየተከታተሉ እንደሆነና አጋጣሚው የሚደግፏቸው ህሙማን የሚጋፈጡትን ችግር ይበልጥ እንዲረዱ እንዳደረጋቸው ገልፀዋል።

ልጃቸው ማቲዎስን በማጣታቸው የገጠማቸውን ጥልቅ ሀዘን ወደ መልካም አጋጣሚ በመለወጥ የካንሰር ህሙማንን ለመርዳት ያቋቋሙት ድርጅት አድጎና ሰፍቶ 43 ሰራተኞችን በመቅጠር 9 ፕሮጀክቶችን እየመራ ሲሆን ላበረከተው መልካም አስተዋፅኦ 6 ዓለማቀፍና 3 አገርአቀፍ ሽልማቶች ተበርክተውለታል።

የድርጅቱ 22ኛ ዓመት ሲከበር የካንሰር ህሙማን አስታማሚዎች ባለሙያ የሚሆኑበትና ገቢ ማስገኛ የሚሆን የወረቀት ዕቃ መያዣ መስሪያ የመረቁት አቶ ወንዱ ሰሚት አካባቢ በሚገኘው መንግስት በሰጣቸው መሬት ከዚህም በላይ ህሙማኑን የሚያግዙ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ይቀረፃሉ ብለዋል።