ሚያዝያ 9 ቀን 1996ዓ.ም የተመሰረተውና በዚህ ዓመት 20ኛ ዓመቱን የሚያከብረው ማቲዎስ ወንዱ – የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ 82 ተማሪዎችንና ወላጆቻቸውን ስለመልካም ተግባራቸው አመስግኗል፡፡
በክረምቱ ወቅት የተለያዩ ገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶችን በማዘጋጀት እና በማዕከሉ የካንሰር ህሙማንን በመንከባከብ የዕረፍት ጊዜያቸውን ለበጎ ዓላማ ያዋሉ ታዳጊዎችና ለመልካም ተግባራቸውም ልጆቻቸውን ወደ ማዕከሉ የላኩ ወላጆች ናቸው ምስጋና የቀረበላቸው፡፡
ለታዳጊዎቹና ወላጆቻቸው ምስጋና ያቀረቡት የማቲዎስ ወንዱ – የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወንዱ በቀለ ልጃቸው ማቲዎስ ከዚህ ዓለም ከተለየ በኋላ ላለፉት 20 ዓመታት ብዙ የካንሰር ታማዎችን ከመደገፍ ጀምሮ በጤናው ዘርፍ ስለሰሯቸው ሥራዎች አብራርተው ታዳጊዎቹ ዓላማቸውን በመደገፍ ለነበራቸው ቆይታ አመስግነዋል፡፡
ሰለማዕከሉ በልጆቻቸው አማካኝነት የተረዱት ወላጆችም በቀጣይ የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ ሶሳይቲውን እንደሚደግፉ የገለፁ ሲሆን ልጆቻቸው በመልካም ተግባር የዕረፍት ጊዜያቸውን በማሳለፋቸው የተሰማቸው ደስታ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከተለያዩ ትምህርት ቤት ተሰባስበው ባላቸው አቅም ሁሉ መፃህፍትን በመሸጥ፣ ሶሳይቲውን በማስተዋወቅ፣ አልባሳትንና ምግብ በመስጠት እንዲሁም ገንዘብ በማሰባሰብ ከትምህርት ነፃ የሆነውን ጊዜያቸውን ለሶሳይቲውና ለካንሰር ህሙማን በጎ ፍቃደኛ ሆነው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ተማሪዎችም ትምህርታቸውን በማይጋፋ መልኩ በቀጣዮቹ ወራትም አገልግሎታቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
በምስጋና መርሐግብሩ ላይ ወሩ በህፃናት ላይ የሚከሰት የደም ካንሰርን በተመለከተ ግንዛቤ ማስጨበጫ እንደመሆኑ የሶሳይቲው ሜዲካል አስተባባሪ ዶ/ር ናትናኤል ትምህርት የሰጡ ሲሆን በሶሳይቲው አማካኝነት ከካንሰር ያገገሙ ታዳጊዎች እና ወላጆቻቸውም በጎፍቃደኛ ተማሪዎቹን አመስግነዋል፡፡
Recent Comments