ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ የዶክተር አይናለም አብርሃ መታሰቢያ መርሐ ግብር አካሄደ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጤና ሳይንስ ኮሌጅ በመምህርነት እና በካንሰር ሕክምና በማገልገል ቀዳሚ የነበሩት ዶክተር አይናለም አብርሃ ባደረባቸው ድንገተኛ ሕመም ሕይወታቸው ማለፉን ተከትሎ ቤተሰቦቻቸው እና የሥራ ባልደረቦቻቸውን በማሰባሰብ ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ መታሰቢያቸውን አከናውኗል፡፡
በጤና ሚኒስቴር የካንሠር መከላከልና መቆጣጠር አማካሪ እና የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ጠቅላላ ጉባዔ ሰብሳቢ ዶ/ር ኩኑዝ አብደላ ዶክተር አይናለም አብርሃ በካንሰር ላይ በከፍተኛ የባለቤትነት ስሜት ታማሚዎቻቸውንም እንደቤተሰብ በማየት ለኢትዮጵያ የካንሰር ህክምና መሻሻል ትልቅ አስተዋፃኦ አበርክተዋል ብለዋል፡፡
በቅንነት፤ ትልቅ ህልም በመሰነቅ ያገለገሉት ዶክተር ዓይናለም በካንሰር ህክምና ጊዜያቸውን ሳያባክኑ ብዙ ሥራ አከናውነው ያለፉ ሰው እንደመሆናቸው ካበረከቱት አስተዋፃኦ አኳያ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መጪው ትውልድ መልካም መሥራት ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስገኝ እንዲገነዘብ ቋሚ ማስታወሻ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ በሥራ ዓለም በተለይም በካንሰር ህክምና አብረዋቸው ያገለገሉ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡ ታላቁን ባለሙያ የሚዘክሩት በካንሰር ላይ የተጀመሩ ሥራዎችን በማስቀጠል መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር ዓይናለም ኅብረተሰቡን ለማስተማር “ ካንሰር ምን፣ እንዴት፣ ከየት ወደየት “ በሚል መፅሐፍ በማሳተም ካንሰርን በተመለከተ ከህክምናም ባለፈ ሁለንተናዊ አግልግሎት ሰጥተዋል ያሉት የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንዱ በቀለ ሁሉን ነገር ሰርቶ ጨርሶ ማለፍ ስለማይቻል መልካም ጅምሮችን መቀጠል እንደሚገባ በማሳሰብ ማቲዎስ ወንዱ- የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ለቤተሰቦቻቸው ያዘጋጀውን የ30,000ብር/ሰላሣ ሺህ ብር/ ስጦታ ለባለቤታቸው አበርክተዋል፡፡ የዶ/ር ዓይናለም ባለቤት መታሰቢያው በመዘጋጀቱ አመስግነው ከልጆቻቸው ጋር በጎ ፍቃደኛ በመሆን ሶሳይቲውን ለማገልገል ቃል ገብተዋል፡፡
ዶክተር አይናለም አብርሃ ሚያዝያ 2013 ዓ.ም ማረፋቸው ይታወሳል፡፡
Recent Comments